የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ S'T IGNATIUS



 ቅዱስ አግናጥዮስ/ ምጥው ለአንበሳ

ቲዎፎሮስ-Theophoros

(from Greek: θεόφορος- ቲዎፎሮስ አግናጥዮስ)

       ከሐዋርያን አበው(Apostolic fathers) መደቡ የሆነ ለባሴ እግዚአብሔር ተብሎ የሚጠራ ሰማዕትና ሐዋርያ ድንቅ አባት ነው። ውልደቱ 30-35 ዓ.ም ሲሆን የተወለደው ክርስቲያኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን ተብለው በተጠሩባት በአንጾኪያ ነው።የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደቀመዝሙሩ ሲሆን በዚች በአንጾኪያ ከቅዱስ ጴጥሮስና ከኤውድዮስ በመቀጠል 3ኛ ጳጳስ በመሆን ለ 40 ዘመናት በታማኝነትና በትጋት ያገለገለ ቅዱስ አባት ነው።

       የነበረበት የመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ለሮማ ቄሳሮች(በእኛ ዓፄ እንደማለት ነው ቄሳር ማለት ሄሮድስና ፈርዖን የሚለውም ዓፄ እንደማለት እንጅ ስም እንዳልሆነ ልብ ይላሉ) እንደ ጸር ይታዮበት እንደ እንስሳ ይታደኑበት የነበረ ጊዜ ስለነበር የአገልግሎት ዘመኑ ቀላል አልነበረም። በተለይ ትራጃን በነገሠ በ12ኛ ዓመት ንጉሡ ድል ማድረጉን አስመልክቶ አማልክቶቼ ብሎ ለሚጠራቸው ምስል አቁሞ ይሰገድላቸው ዘንድ ያውጅ ስለነበር ለዚህ አዋጁ የዚህ ጽኑእ አባት ትምህርት እረፍት አልሰጠውም(98-117 የትራጃን ንጉስ ዘመን)። ስለሆነም በክስ አሳስሮ አንተ ርጉም ርኩስ ስለምን እንዲህ ታደርጋለህ ሲለው አግናጥዮስ ቴኦፎሮስን ርጉም የሚለው ማንም የለም ባለው ጊዜ ቴኦፎሮስ ምን ማለት ነው ሲል ንጉሡ ጠየቀው እርሱም ቴኦፎሮስ ማለት ክርስቶስ በውስጡ ያለው እርሱ ነው ቴኦፎሮስ በማለት እርሱ ስለራሱ ሳይሆን ስለ በእርሱ ክርስቶስ የሚኖር መሆኑን ነገረው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስ በእኔ ይኖራል እንዳለ። በዚህን ጊዜ ንጉሡ ጽናቱን በምስክርነቱ ስለተረዳ ወደ ሮም ለተራቡ አናብስት ይጣል ዘንድ አስጋዘው በቤተክርስቲያናችንም ለአናብስት በመጣሉ ምጥው ለአንበሳ መባሉም ለዚህ ነው።

       ይህ አባት ለክርስቶስና ለክርስትናው የነበረው ቅንአት ልዮ ነበር። ወደ ሰማዕትነት ስፍራው እየሄደ የወገኖቹን ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር እየተመለከተ እንዲህ ይላቸዋል "እኔ ክርስቲያን ተብየ ብቻ የምጠራ ሳልሆን በእውነት ሆኜ መገኝት አለብኝ"። በመንገድም በግዞት ላይ እያለ የጌታችንን "ኢየሱስ ክርስቶስ" የሚለውን ስም ደጋግሞ ይል ነበር ወታደሮቹም የሚሰጠውን ምስክርነት ያቆም ዘንድ ስቃዮን ሲያበዙበት "የክርስቶስ ስም በአንደበቴ ብቻ ሳይሆን በልቤ ውስጥም ተጽፏል ስለዚህ ይህን ስም ለመተው አልችልም" አለ፡፡ የአሕዛብም በዓል በሚከበርበት (December 21) ወደ ፍላቪያ አምፊቴያትር (Colosseum) ለአናብስት ይጣል ዘንድ ገባ። የተራቡ ሁለት አናብስትም ወጥተው ከጥቂት አጥንቶቹ በስተቀር በአሰቃቂ ሁኔታ ሥጋውን ተቀራመቱት እንዳለውም የአናብስቱ ጥርሶች ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ ሆነለት እራሱንም ለክርስቶስ የንጹሕ ስንዴ ሕብስት አድርጎ አቀረበ። እናዳለውም በወርቅ የተጻፈ "ኢየሱስ ክርስቶስ" የሚል ስም ተረፍ ከነበረው ልቡ ውስጥ ተጽፎ ተገኘ፡፡ በምስራቅ ኦርቶዶክስና በእኛ እውቅ የሆነ የሚነገር ትውፊት አለ ጌታ ለመንግሥቱ ምሳሌ አድርጎ ያስተማረበት ጌታ ያቀፈው እርሱ ቅዱስ አግናጥዮስ እንደሆነ ይነገራል፡፡ማቴ.18÷3::ስለዚም ነው እግዚብሔር የተሸከመው የሚልም መጠሪያ የተሰጠው (God Bearer) ይህም አባት የተለያዩ ጽሑፎችን የጻፈ ሲሆን ለቅዱስ ፖሊካርፐስ የጻፈውን ጨምሮ ወደ ስድስት የሚደርሱ ናቸው በእነርሱም ጥብቅ የዶግማ ትምህርቶችን አስተምሯል፡፡ የቅዱሱም አጽም በ January 29 ወደ አንጾኪያ የፈለሰ ሲሆን ከብዙ ዓመታት ቡኀላ February 1 በ637 ወደ ሮም ተመልሶ san Clemente ቤተክርስቲያን ተቀምጧል፡፡

   ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የዚህን ቅዱስ አባት እረፍት ታኅሳስ 24 ታስበዋለች በእውነት የቅዱስ አግናጥዮስ ለባሴ ክርስቶስ በረከቱ ይድረሰን።

     Theophorus/Christophorus ማለት የግሪክ ቃል ሲሆን The bearer of God/Christ. እግዚአብሔርን የተሸከመ ማለት ነው።

✥ሰላም ለዝክረ ስምከ

     በሰማይ በምድር ለዘለአለም በማይዘነጋና በማይጠፋ ወርቅ ቀለም በእግዚአብሔር ዘንድ ለተጻፈው ክቡር ስምህ ሰላምታ ይገባል። ቅዱስ አግናጥዮስ ሆይ ተጠርቶ የማይዘነጋውን ከማር የሚጣፍጥ መልካም ስምህን በመውሰድ ዘወትር በመጥራት አንተን አማላጅ አድርጌሃለሁ። ስለዚህ ትሩፋትህ የተትረፈረፈ ደገኛው መምህር ሆይ ምንም ከጽድቅ የተራቆትኩ ብሆንም በአማላጅነትህ ባህረ እሳትን እንድታሻግረኝ ተማጽኜሃለሁ።

እንኳን የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖትን በዓለ ልደት የሰማዕቱና የሐዋርያውን የቅዱስ አግናጥዮስ በዓለ እረፍት ለምናስብባት ዕለት አደረሰን! አምላካችን በጸሎታቸው ይርዳን በበረከታቸው ይጎብኘን!

No comments:

Post a Comment