ሰማዕቷ ቅድስት ቅፍሮንያ
ስሟ ኦርያና የተባለች 50 ደናግል መነኮሳይያትን እመ ምኔት ሆና የምትመራ ደገኛ እኅት አለቻት፡፡ ቅድስት ኦርያናም እኅቷን ቅድስት ቅፍሮንያን ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ቅዱሳት መጻሕፍትን እያስተማረች አሳደገቻት፡፡ ቅድስት ቅፍሮንያ እስከ ሁለት ቀን ድረስ የምትጾም ተጋዳሊት እስከሆነች ድረስ ትሩፋት መሥራትንና በጎ ተግባራትን አበዛች፡፡
በወቅቱም ከ470,000 በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖችን በሰማዕትነት የሰየፈው ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ በዓለም ላይ የጣዖት አምልኮን ባወጀ ጊዜ በገዳም ያሉ ደናግልም ወሬውን ሲሰሙ ወጥተው በመሄድ ተሠወሩ፡፡ እመ ምኔቷ ቅድስት ኦርያና እኅቷ ቅድስት ቅፍሮንያ ግን ብቻቸውን ቀሩ፡፡ በማግሥቱም ጭፍሮቹ መጥተው እመ ምኔቷን ያዟት ነገር ግን ቅድስት ቅፍሮንያ ‹‹እርሷ አርጅታለችና በእርሷን ትታችሁ እኔን ውሰዱኝ›› አለቻቸውና ይዘው ወደ መኮንኑ ወሰዷት፡፡ እመ ምኔቷም ተከተለቻቸው፡፡ መኮንኑም ለአማልክት እንድትሠዋ ብዙ በማባበል ቃልኪዳን ገባላት፡፡ ቅድስት ቅፍሮንያ ግን ቃልኪዳኑንም ሆነ አምልኮቱን አቃለለችበት፡፡ ትእዛዙንም እንዳልተቀበለችው ባየ ጊዜ ጽኑ ድብደባ አደረሰባት፡፡ ዳግመኛም ልብሷን ገፈው ሥጋዋን ግልጥ ባደረጋት ጊዜ እመ ምኔቷ ቅድስት ኦርያና ጮኻ መኮንኑን ‹‹አንተ ከሃዲ ይህችን ታናሽ ብላቴና እንሠቃየሃትና እንዳጎሳቆልካት እግዚአብሔር ያጎሳቁልህ›› ብላ ረገመቸው፡፡ በዚህም ጊዜ መኮንኑ እጅግ ተቆጥቶ ቅድስት ቅፍሮንያን አሥሮ በመንኮራኩር ውስጥ አሠቃያት፡፡ ሰውነቷንም በብረት መጋዝ ሠነጠቃት፡፡ እርሷም ወደ እግዚአብሔር በጮኸች ጊዜ ወዲያው ከሕመሟ ሁሉ ድና ምንም ጉዳት እንዳላገኛት ሆነች፡፡
ዳግመኛም መኮንኑ የቅድስት ቅፍሮንያን ምላሷንና ሕዋሳቶቿን ሁሉ ቆራረጣቸው፡፡ ጥርሶቿንም ሰበራቸው፡፡ አሁንም ጌታችን ፍጹም ጤነኛ አድርጎ ያለሕማም አስነሣት፡፡ መኮንኑም እርሷን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሷን በሰይፍ አስቆረጣትና የሰማዕትነቷ ፍጻሜ ሆኖ የድል አክሊልን ተቀዳጀች፡፡ አንድ ባለጸጋ ምእመንም መጥቶ የቅድስት ቅፍሮንያን ሥጋ ወስዶ ባማሩ የሐር ልብሶች ገንዞ በወርቅ ሣጥን አኖራት፡፡ ከሥጋዋም ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተገለጡ፡፡ ረድኤት በረከቷ ይደርብን በጸሎቷ ይማረን!
No comments:
Post a Comment